የሥራ ሥነምግባር (Work Ethics)
- Ayalew-kuma
- Nov 11, 2019
- 2 min read
የሥራ ሥነምግባር ማለት አንድ ሠራተኛ በሥራው እንዲረካ፣ ብቃቱ እንዲጎለብት እና ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ መለኪያ መስፈርቶች ወይም ሕጎች ስብስብ ነው፡፡ የሥራ ሥነምግባርን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ እነዚህም ግላዊ እና ሥራ ተኮር /ቀጥታ ከሥራ ጋር በተገናኘ/ ሲሆኑ የተወሰኑት የሥራ ሥነምግባሮች ግላዊ ሆነው በራሳቸው በግለሰቦች በጎ ፈቃድ የሚፈጸሙ እና ከውስጣቸው የሚመነጩ ናቸው፤ መገለጫዎቹም፡ ለሰዎች እና ለሥራው ተገቢ ክብር መስጠት፣ ተለማጭ (Flexible) መሆን፣ ቀጠሮ አክባሪ መሆን፣ የአቋም ሰው መሆን፣ የሚሉት ሲሆኑ ከሥራው ጋር በተገናኘ ሰራተኞች መሆን የሚጠበቅባቸውን በተመለከተ ደግሞ ሥራው በራሱ የሚያስገድዳቸው ሁኔታዎችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ መገለጫዎችም፡ በምስጢር መያዝ ያለባቸውን ነገሮች በሚስጢር መያዝ ለደንበኞች ትሁት እና ቅን አገልጋይ መሆን አዲስ አሰራርን እና ተግባርን ለመቀበል ራስን ማዘጋጀት የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በሥራ ሥነምግባር ሥራው፣ ሰራተኛው እና የመስሪያ ቦታው /ከነቁሳቁሱ/ በዋናነት የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ደ;ግሞ ሰራተኛው ዋናው እና እጅግ አስፈላጊው አካል ነው፡፡ ምክንያቱም ማሰብ፣ ማገናዘብ፣ መማር እና ሥራውን መስራት የሚችለው ሰው ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ሥራውን በተገቢ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን የሥራ ሥነምግባር ማዘጋጀት እና በዚያ መመራት ይጠይቃል፡፡ ከሥራ ጋር ተያያዥ የሆኑ የሥነምግባር ችግሮች · ሰዓት አለማክበር · · · · · · ደንበኞችን መዝለፍ፣ ማንገላታት እና ተገቢ አገልግሎት አለመስጠት፣ ለሥራው ተፈላጊ እውቀት እና ክህሎት አለመኖር ወይም አለመጠቀም፣ የመስሪያ እቃዎችን በአግባቡ አለመያዝ እና ማባከን፣ የአሰራር ሥርዓት ሕጎችን አለማክበር፣ ለሥራው ተገቢ ክብር አለመስጠት ለድርጅቱ ወይም ለመስሪያ ቤቱ ታማኝ አለመሆን የተሻለ የሥራ ሥነምግባር የሚከተሉትን ነገሮች ማሟላት አለበት፡ ሀ. በስራ ላይ መገኘት:- በሥራ ላይ ተገኝቶ መስራት ለራሱ ለሠራተኛውም ሆነ ለቡድኑ ውጤታማነት አስፈላጊ ሲሆን በሥራ ላይ በመገኘት ውጤታማ ሥራ መስራት ማለት፡· ለዋናው ሥራ ከፍተኛ ትኩረት እና ቅድሚያ መስጠት፣ · የሥራ ቅደም ተከተሎችን ጠንቅቆ ማወቅ፣ · ከሥራ ሰዓት ዘግይቶ አለመግባት እና ቀድሞ አለመውጣት፣ · የሥራ ጊዜን ለተገቢው ሥራ ማዋል፣ · በችግር ከስራ ስንቀር ለቅርብ ኃላፊ ማሳወቅ እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡ ለ. ተገቢ ባሕሪ ማሳየት:- የሚሰሩበትን መስሪያ ቤት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችለውን ተፈላጊ ባሕሪ ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ባሕሪያት ምንድን ናቸው? · ሀቀኝነት፣ ·ታማኝነት፣ ·በሥራ ተፈላጊነት፣ ·በሥራ ተጽእኖ ፈጣሪነት፣ · የአቋም ሰው መሆን፣ ·ተነሳሽነት፣ ሥርዓት አክባሪነት እና ·ሃላፊነትን መውሰድ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ሐ. በቡድን ሥራ ማመን:- የቡድን ሥራ ለአንድ መስሪያ ቤት በጣም አስፈላጊ ሲሆን መገጫዎቹም፡·የሌሎችን መብት ማክበር፣ ·ተግባቢ መሆን፣ ·ታጋሽ እና ፅኑ መሆን፣ ·የአገልግሎት ሰጭነት አመለካከት መኖር፣ ·ከሌሎች ለመማር እና ያለንን ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ መሆን፣ ·ሚስጢር መጠበቅ እና ·ለሥራ እንጂ ተገቢ ላልሆነ ጥቅም ራስን አለማስቀደም የሚሉት ይገኙበታል፡፡ መ. ተገቢ አለባበስን መጠቀም:- አለባበሳችን ለሥራ ምቹ የሆነና የመስሪያ ቤቱ ሠራተኛ ለመሆናችን የሚገልጽ እንደሁኔታው የሥራ /የደንብ/ ልብስ መልበስ ያስፈልጋል፡፡ ሠ. አመለካከት:- ለሥራ በተሰማራንበት ቦታ አዎንታዊ አመካከት፣ በራስ መተማመን እና ለራሳችን ያለንን ግምት ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ረ. ምርታማነት:- ምርታማ ለመሆን ጤናማ የሥራ ቅደም ተከተል፣ ተገቢ የሥራ መሣሪዎች አጠቃቀም፣ ንፁህ የሥራ ቦታ እና የመሳሰሉት መሟላት አለባቸው፡፡ ሰ. ተገቢ የሥራ ክህሎት:- ለመስሪያ ቤቶች ውጤታማ የሰዓት አጠቃቀም እና ተገቢ የሥራ ክህሎት አስፈላጊ ግብዓቶች ሲሆኑ እነዚህ ነገሮች የግል እና የመስሪያ ቤታችንን ሥራ በብቃት ለመወጣት ጠቃሚ ናቸው፡፡ ለዚህ መገለጫ የሚሆኑት፡·ወደ አዲስ መስሪያ ቤት ስንገባ ለቦታው ተፈላጊ የሆኑ የሥራ ክህሎቶችን መለየት፣ ·በሥራ ላይ የሚያስቸግሩን ነገሮች ሲኖሩ መጠየቅ፣ ·ለሥራው የበለጠ ጠቃሚ የሆነውን ቅድሚያ መስጠት እና ·ያከናወንነውን እና ያላከናወንነውን ነገር ለመለየት እና የቀረንን ለማስተካከል የሚያግዙ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ፡፡ ሸ. ተግባቦት:- ውጤታማ ግንኙነት መፍጠር እና ሌሎች ለእኛ እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን እኛም ለሌሎች ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ቀ. መተባበር:- መልካም የሥራ ግንኙነት መፍጠር፣ የበላይ አካል ትእዛዝን መጠበቅ/ማክበር፣ ግጭቶችን በውይይት መፍታት እና አጠቃላይ ችግር ፈቺ ሆኖ መገኘት አለብን፡፡ በ. ከበሬታ:- በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ላሉ የበላይም ሆነ የበታች ሠራተኞች በእኩል ከበሬታ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ ||ከስነ-ምግባር መከታተያ ክፍል

Comments